Fana: At a Speed of Life!

የሌላ ደንበኛ ሂሳብን ‘የእኔ ነው’ በማለት 12 ሚሊየን ብር ሊያዘዋውር የሞከረው ተከሳሽ በእስራት ተቀጣ

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሌላ ደንበኛ ሂሳብ ‘ባለቤት ነኝ’ ብሎ 12 ሚሊየን ብር ሊያዘዋውር ሲሞክር በባንኩ ሰራተኞች የተያዘው ተከሳሽ በአምስት ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ወሰነ።

ተከሳሹ መምህር መንግስቱ ተመስገን በወንጀል ምርመራ ሂሳቡ የታገደበትን ተማም መሃር የተባለ ግለሰብ ስም ተመሳስሎ የተዘጋጀ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በመያዝ መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ በገፈርሳ ጉጂ ክፍለ ከተማ በሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡራዩ ቅርጫፍ በመሄድ ለባንኩ ባለሙያዎች ተማም መሃር የተባለ ቡና ላኪ ባለሃብት እንደሆነ በመግለጽ እንደተዋወቃቸው በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

ተከሳሹ በሌላ ቅርንጫፍ ከ12 ሚሊየን በላይ ገንዘብ ያለው ሂሳብ መክፈቱን በመግለጽ እንዲሁም “ያንን ሂሳብ ዘግቼ እናንተ ቅርጫፍ አዲስ ሂሳብ ልክፈትና 12 ሚሊየን ብሩን በዚህ ቅርጫፍ ወደ ምከፍተው ሂሳቤ አዘዋውሩልኝ ” በማለት መጠየቁ ተመላክቷል፡፡

በባንኩ አሰራር መሰረት የጠየቀው የገንዘብ መጠን ከፍ ያለ በመሆኑ የባንኩ ማናጀር ማረጋገጫ መስጠት ስላለበት ባለሙያዎቹ ወደ ባንኩ ማናጀር ይልኩታል፡፡

የባንኩ ማናጀርም በቀረበው ጥያቄ መነሻ መንጃ ፍቃድ ወይም ፓስፖር፣ ቪዛ እንዲያሳየው ሲጠይቀው ተከሳሹ አለመያዙን መልስ የሰጠ ሲሆን የባንኩ ማናጀር ተማም መሃር በተባለ ግለሰብ ስም የተከፈተው ሂሳብ ባለቤት መሆኑንና አለመሆኑን ለማረጋገጥ ኮምፒዩተር ከፍቶ ሲመለከት ሂሳቡ በወንጀል ምርመራ እንዳይንቀሳቀስ የታገደ የሌላ ሰው ሂሳብ መሆኑን በማረጋገጥ ከሰራተኞቹ ጋር የባንኩን ጥበቃ ጠርቶ ተከሳሹን በማስያዝ ለፀጥታ አካላት አሳልፎ መስጠቱ በክስ ዝርዝሩ ላይ ተጠቅሷል።

ተከሳሹ በቁጥጥር ስር ከዋለና ምርመራ ከተደረገበት በኋላ የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ቅርጫፍ ጽ/ቤት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ ላይ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ጠቅሶ ክስ አቅርቦበታል።

ተከሳሹ የክሱ ዝርዝር ከደረሰው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃል በመስጠቱ፤ ዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክርና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሹ እንዲከላከል በሰጠው ብይን ተከሳሹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል ባለመቻሉ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቶበታል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን መርምሮና ይዞ ተከሳሹን በአምስት ዓመት ጽኑ እስራትና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.