ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በብሪክስ ማዕቀፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር መከሩ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ የሁለትዮሽ ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና የደቡብ አፍሪካ የብሪክስ ቢዝነስ ካውንስል የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗን ተከትሎ በሀገር ውስጥ በተለያዩ ተቋማት አጋዥ አደረጃጀቶች ተፈጥረው ከአባል ሀገራቱ አቻ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ጥረት እያደረገች መሆኗ ተገልጿል።
በትብብር ማዕቀፉ ውስጥ በስፋት ትኩረት ከሚሰጥባቸው መስኮች አንዱ በሀገር ደረጃ የግል የቢዝነስ እና ማህበራዊ ዘርፎችን በማደራጀት እና በብሪክስ ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ ተሳትፎን ማስፋት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የራሷን የብሪክስ ቢዝነስ ካውንስል አቋቁማ ወደ ሥራ በመግባት አደረጃጀቱንና ተያያዥ መዋቅራዊ ሥራ ለማጠናቀቅ ከቀድሞ ብሪክስ አባል ሀገራት ቢዝነስ ካውንስል የአሠራርና አደረጃጃት ልምዶችን እየቀመረች እንደምትገኝ ተጠቁሟል።
በዚህም የደቡብ አፍሪካ እና የኢትዮጵያ ብሪክስ ቢዝነስ ካውንስል በበይነ-መረብ አማካኝነት የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውን በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።
የሀገራቱ የቢዝነስ ካውንስል ቡድኖች በውይይታቸው÷ በቀጣይ በቦርድ ደረጃ መነጋገርና መመካካር ስለሚችሉበት እንዲሁም በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ የሁለትዮሽ ትብብርን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡