Fana: At a Speed of Life!

በሀሰተኛ ሰነድ የአፈር ማዳበሪያ በማዘዋወር የተከሰሰው ግለሰብ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በሀሰተኛ ሰነድ ሲያዘዋውር የተያዘው ተከሳሽ በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ተወሰነ፡፡

በተከሳሹ ላይ ዛሬ ከሰዓት የጽኑ እስራትና የገንዘብ መቀጮ ቅጣት የወሰነው የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሸገር ከተማ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ዐቃቤ ህግ አብርሃም ዘሪሁን በተባለ ተከሳሽ ላይ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ጠቅሶ ባሳለፍነው 2016 ዓ.ም ዝርዝር ክስ አቅርቦበት ነበር።

በዚህ በቀረበው ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው ተከሳሹ ከግብርና ሚኒስቴር ለሀረሪ ክልል አርሶ አደሮች የሚውል በዘኢላ ህብረት ስራ ማህበር በሚል የተሰጠን የወጪ ደረሰኝ ሰነድን ግርማ ወልደ ጎርጊስ በሚል ስም ሀሰተኛ የወጪ ሰነድ አዘጋጅቶ የጉዞ አቅጣጫውን ቀይሮ በተሳቢ ተሽከርካሪ 400 ኩንታል ማዳበሪያ ጭኖ በህገወጥ መንገድ ወደ ደብረ ብርሃን ሲጓዝ በግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 7:00 ሰዓት ላይ በሸገር ከተማ በለገዳዲ ለገጣፍ ክፍለከተማ ልዩ ስሙ አባ ኪሮስ እየተባለ በሚጠራው ኬላ አካባቢ ሲደርስ በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር የዋለ መሆኑን ዐቃቤ ህግ በክስ ዝርዝሩ ላይ ጠቅሷል።

ተከሳሹ በዚህ መልኩ የቀረበበት ክስ ዝርዝር በችሎት ከደረሰው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸሙን ጠቅሶ የሰጠውን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የሰው ምስክርና ሀሰተኛ ሰነድ በማስረጃነት ለችሎቱ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሮ በክሱ ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን አረጋግጫለሁ በማለት ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከል ብይን የሰጠ ሲሆን÷ተከሳሹ ባቀረበው የመከላከያ ማስረጃ የዐቃቤ ህግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል አለመቻሉ ተገልጾ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶበታል፡፡

ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን መርምሮ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በዋለው ቀጠሮ በተከሳሹ የቀረቡ የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን በመያዝ ተከሹን በ3 ዓመት ከ3 ወራት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በህገወጥ መንገድ ሲያዘዋውር የተያዘው 400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.