Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያና ሶማሊያ ድንበር የሚገኘው ጦር በአስተማማኝ የዝግጁነት ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያና ሶማሊያ ድንበር የሚገኘው ጥምር ጦር በአስተማማኝ የዝግጁነት ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የጥምር ጦሩ አመራሮች በወቅታዊ የሠላም ሁኔታ ላይ ውይይት አካሂደዋል።

በዚሁ ወቅት በመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ የሀይል ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው÷በቀጣናው የሚገኘው ጥምር ጦር በአስተማማኝ የዝግጅት ቁመና ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውን ገልፀዋል።

የአየር ኃይሉ ምክትል አዛዥ ለአየር ኦፕሬሽን ብርጋዲየር ጄነራል ተስፋዬ ለገሰ በበኩላቸው÷ከአየር ኃይሉ እውቅና ውጪ በቀጣናው ሰማይ ላይ ለሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን ብለዋል።

የሀገርን ዳር ድንበር ከየትኛውም ወራሪ ኃይል አስከብሮ በቀጣናው ሰላምን ለማስፈን የጥምር ሃይሉ አካል በመሆን እየሰሩ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የሶማሌ ክልል ፖልስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አብዲ አሊ ዝያድ ናቸው፡፡

ከውይይቱ በኋላም የሁለተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አጠቃላይ የወትሮ ዝግጁነት ደረጃ ምልከታ መደረጉን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.