Fana: At a Speed of Life!

በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ሕዝባዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለው ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚጠይቁ ሕዝባዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።

ሰልፈኞቹ በክልሉ መንግሥት እያካሄደ ያለውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ የሚደግፉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡

በሰልፉ ከተላለፉ መልዕክቶች መካከልም ÷ ለክልላችን የሚያስፈልገው ጦርነት ሳይሆን ሰላምና ልማት ነው፣ መንግሥት ሕግ በማስከበር የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ሊያስጠብቅ ይገባል፣ መከላከያ ሠራዊታችን፣ የፌዴራልና የክልላችን የጸጥታ ኃይሎች ለከፈሉት ዋጋ ክብር እንሰጣለን የሚሉትን ጨምሮ ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

የሐይማኖት አባቶችን ጨምሮ የመንግሥት ሠራተኞች እና ተማሪዎችን ባካተተው በዚህ ሰልፍ ላይ ደሴ ከተማ የሰላም አምባሳደር መሆኗን የሚያስተጋቡ መፈክሮች እየተሰሙ ነው።

የሁለቱም ከተሞች የሰልፉ ተሳታፊዎች ሰላም ከሌለ ልማት አለመኖሩን አንስተው÷ የመንግስት አገልግሎትንም በፍትሐዊነትና በቅልጥፍና ተደራሽ ለማድረግ ስለማይቻል ሰላም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ለዚህም መንግስት የጀመረውን ሰላም የማስከበር  ሥራ አጠናክሮ ይቀጥል፤ እኛም የሚጠበቅብንን ሁሉ ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በጫካ ያሉ ወገኖች ለሕዝባቸው እረፍት እንዲሰጡም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።

የሰልፉ ተሳታፊ ተማሪዎችም በሰላም ትምህርታችንን መከታተል እንፈልጋለን፤ ጦርነትና ግጭትም ሊበቃ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በሚታየው ግጭት ምክንያት በሚሊየን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው አግባብ አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተዘጉ ትምህርት ቤቶችም ተከፍተው ወደ መማር ማስተማር ስራ እንዲገቡ ጠይቀዋል።

በስንታየሁ አራጌ፣ አለባቸው አባተ እና ከድር መሐመድ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.