Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ማቋቋም አተገባበር ላይ የማህበረሰብ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ማቋቋምና ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀል አተገባበር ሂደት የሕብረተሰቡ ሚና ምን መሆን እንዳለበት የሚመክር መድረክ በመቐለ ከተማ ተካሄደ።

በምክክሩ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የትግራይ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ ኮሌኔል ኪሮስ ወልደስላሴ÷ የቀድሞ ተዋጊ ሴቶች፣ የወጣቶችና አካል ጉዳተኞች የተለየ ትኩረትና ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተሳተፉ መሆኑን ገልፀዋል።

በፕሮግራሙ ተሳትፈው ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች የሚሰጣቸውን የመልሶ መቀላቀል ክፍያ በአግባቡ ስራ ላይ ሊያውሉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በየአካባቢው ማህበረሰቡ ለተመላሾች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአርበኞች ኮሚሽነር አቶ ናስር መምሁር በበኩላቸው÷ ክልሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የአርበኞች ኮሚሽን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች በሚፈጠርላቸው መልካም አጋጣሚና በተሰጣቸው የመልሶ መቀላቀል ገንዘብ የተለያዩ ሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑም አስገንዝበዋል፡፡

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መድረክ በዚህ መድረክ የወጣችና ሴቶች ተሳትፎ እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራዎች ምን መሆን እንዳለባቸው ምክክር መደረጉን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

በውይይቱ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተውጣጡ የሥራ ሀላፊዎች፣ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች፣ የሀገር ሽግሌዎች፣ የወጣቶችና ሴቶች፣ የቀድሞ ተዋጊ የነበሩ ቤተሰቦችም ተሳትፈዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.