መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት ህብረተሰቡ ሊያግዝ እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት ህብረተሰቡ ሊያግዝ እንደሚገባ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ አስገነዘቡ።
በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በደሴ ከተማ ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት የአቶ ሣሙኤል ሞላልኝ፥ አሁን ያለው የሰላም እጦት ከዚህ በፊት ሲቀነቀን የነበረው የዘረኝነት ስሜት ፈንድቶ ያመጣው ቀውስ ነው ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ይነሱ የነበሩት የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚችሉበትን መንገድ በመቀልበስ በጦርነት እና በመሳሪያ በማድረግ ሰላምን የነሳ ችግር መፈጠሩ የሚያሳዝን ነው ብለዋል፡፡
በግጭቱ ምክንያት ተማሪዎች እንዳይማሩ፣ ሠራተኛው እንዳይሰራ፣ ገበሬው ምርቱን እንዳያመርት አጠቃላይ የክልሉን ኢኮኖሚ የማድቀቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ከጦርነት ወጥቶ ወደ ሰላም መምጣት ያስፈልጋል ያሉት ከንቲባው፥ ማህበረሰቡ እጅና ጓንት ሆኖ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።
መምህራን እንዲያስተምሩ፣ ተማሪዎች ነጋቸውን በዛሬ ትምህርት እንዲሰሩ ለማድረግ ሰላም ያስፈልጋልና መንግስትን ማገዝ ይገባልም ነው ያሉት።
ሰላም ሲሆን የህዝብ ጥያቄን መመለስ እንደሚቻል ጠቅሰው፥ ፅንፈኞች ፊታቸውን ወደ ሰላም አዙረው ለህዝቡ እረፍት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ግጭትን በማራዘም የክልሉን ኢኮኖሚ ከማዳከም የዘለለ ጥቅም ስለሌለው መንግስት አሁንም ደጋግሞ ለሰላም እጁን ይዘረጋል ብለው፥ የመከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የፀጥታ ኃይሉን አመስግነዋል።
የደሴ ከተማ የሀይማኖት ተቋማቶች ህብረት አባቶች፥ ሰላም ከሌለ አርሶ መዝራት፣ ወልዶ መሳም፣ ተምሮና ሰርቶ መግባት ስለማይቻል ለሀገራችን ሰላም መሆን መስራት ይገባል ብለዋል።
ለራሳችን ሰላም ሆነን ለሌሎች የሚተርፍ ሰላም እንዲኖረን ልንሰራ ይገባልም ነው ያሉት።
የንፁሀንን ደም በከንቱ ማፍሰስ፤ በወንድማማችነት መካከል የሚደረግ ጥል በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት የለውምና መሳሪያ ይዘው ጫካ ያሉ ወንድሞቻችን መንግስት ያደረገውን ጥሪ ተቀብለው በጠረጴዛ ዙሪያ ችግራቸውን እንዲፈቱ ጥሪ እናስተላልፋለንም ብለዋል።
ሰላም ለኢትዮጵያ፤ ጦርነት ይቁም ያሉት አባቶች፥ መንግስት የሚከተለውን የሰላም አመራጮች ሁሉ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
በአለባቸው አባተ እና ስንታየሁ አራጌ