ከህዝባችን የተሰማውን የሰላምና የልማት ጥያቄ ለመመለስ ተዘጋጅተናል – የጎንደር ከተማ አስተዳደር
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከህዝባችን የተሰማውን የሰላምና የልማት ጥያቄ ለመመለስ ተዘጋጅተናል ሲሉ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።
ከንቲባው በዛሬው ዕለት በጎንደር ከተማ በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራትንና የሰላምን መረጋገጥ በመደገፍ የተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው ይህንን ያሉት።
የልማት ጥያቄ መብትና ተገቢ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ የሀገር ሽማግሌዎች እየመከሩ የገጠሙንን ችግሮች በጋራ እንዲፈቱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በከተማዋ ህዝቡን ሲያስመርርና ቅሬታ እንዲያቀርቡ ሲያደርግ የቆዩ ችግሮች መኖራቸውን አስታውሰው፤ በአሁኑ ሰዓት የተጀመሩ የከተማ የልማት እንቅስቃሴዎች ጥሩ ተስፋ የሰነቁ ናቸው ብለዋል።
አሁን ያለው የሰላም ጭላንጭል የበለጠ እንዲያበራ የከተማዋ ማህበረሰብ ሊያግዝ ይገባል፤ የከተማችን የሰላም ደወል የልማት ጥሪ ዛሬ ከህዝቡ ዘንድ ተሰምቷል እኛም ጥያቄውን ለመመለስና በቁርጠኝነት ለመስራት ተዘጋጅተናልም ነው ያሉት።
ሰላምና ብልፅግና የፖለቲካ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነውና በቅሬታ ውስጥ ያላችሁ ወገኖችም ለሰላምና በጋራ ለማደግ እጃችንን ዘርግተንላችኋልና ወደ ሰላም ተመለሱ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በትጥቅ ትግል ላላችሁም እንደ ባህላችን በሽምግልና በውይይት ተመካክረን ከተማችንን እንድንለውጥ ጥሪ እናቀርባለን፤ የእምነት አባቶችም ጦርነትና መገዳደል አስከፊ መሆኑን አበክረው ማስተማር ይኖርባቸዋል ሲሉ ጠይቀዋል።
የሀገር ሽማግሌዎችም እስካሁን ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነው፤ የተሟላ ሰላም እስከሚገኝ ያላሰለሰ ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ እንዲሁም የከተማዋ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ከተማዋ ያሉባትን ችግሮች በመቅረፍ ሂደት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የከተማዋ ወጣቶች፣ ሴቶችና መላው ነዋሪም ለከተማዋ ሰላምና ልማት እንዲተባበሩ ጥሪ ቀርቧል።
በሙሉጌታ ደሴ እና ሹመት አለማየሁ