የአንካራው ስምምነት የጠንካራ ዲፕሎማሲ ውጤት ነው – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግስት ጋር በቱርክ አንካራ ያደረገችው ስምምነት የጠንካራ ዲፕሎማሲ ውጤት መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ እንዳሉት፤ የባህር በር ለማግኘት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኩል የተደረገው ተግባር ድፍረት እና ጥበብ የተሞላበት ነው።
ጥያቄው ህጋዊ መሰረት ያለው መሆኑን ገልጸው፤ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ መስኮች የተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያ የማንሰራራት ምዕራፍ ውስጥ መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ከሶማሊያ ጋር በአንካራ የተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ሚና ለማሳነስ የሚጥሩ ጠላቶችን ያሳፈረ መሆኑን ተናግረዋል።
ለሶማሊያ ሉዋላዊነት እና አንድነት መከበር ኢትዮጵያውያን የከፈሉትን መስዋዕትነት ለማሳነስ የተደረገውን ጥረት መክሸፉን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ ተገቢ መሆኑን ለዓለም ያሳመነና ተሰሚነቷን ከፍ ያደረገ ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።
ስምምነቱ የውክልና ጦርነት ኢትዮጵያ ላይ ለማድረግ የሚፈልጉ ጠላቶችን ያሳፈረ ነበር ማለታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።