ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የልማት እንቅስቃሴዎችን መጎብኘታቸውን ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የልማት እንቅስቃሴዎች እየጎበኙ ነው፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ እየተሰሩ ያሉ የእንስሳት እርባታ፣ የኮሪደር ልማትና የመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥን ጎብኝተዋል፡፡
ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በክፍለ ከተማው እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች በሀገር ደረጃ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለሚሰሩት ስራዎች ምሳሌ ነው፡፡
በጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የተመራ ቡድን ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሶዶ ከተማ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችንና የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤትን ጎብኝቷል።
በጉብኝቱም በወላይታ ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ የሚበረታቱና ከአካባቢው አልፎ ለሀገር የሚያበረክተዉ አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።
በተለይ የብዙ ሀኪሞች መፍለቂያ የሆነዉን የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት ከሚታወቅበት በተጨማሪ በቴክኖሎጂው ዘርፍም ይበልጥ አጠናክሮ መስራት እንዳለበትም ዶክተር መቅደስ አመላክተዋል።
በተመሳሳይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በአፋር ክልል የተለያዩ ወረዳዎች በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በዚሁ ወቅት ሚኒስትሯ እንዳሉት፥ ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ልማት በማስገባት ከተቻለ የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብርን በተሟላ ደረጃ ማከናወን የሚያስችል አቅም አለው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በክለሉ ኮንታ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።