Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ተሃድሶ ስልጠና መግባት ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ተሃድሶ ስልጠና ማዕከል የማስገባት ስራ በይፋ መጀመሩን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሕዳር 6 ቀን 2017 የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ በማስረከብ የተሃድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በዕለቱም የአፋር ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በማስረከብ ለሰላምና ልማት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በመሆኑም በክልሉ ካሉት 1 ሺህ 750 የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል የመጀመሪያው ዙር ሰልጣኞች ወደ አብዓላ የተሃድሶ ስልጠና ማዕከል የማስገባት ስራ በይፋ ተጀምሯል።

የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የፕሮግራም ዕቅድና ክትትል ዳይሬክተር ኮሎኔል በላይ አበበ ፥ በክልሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሃድሶ ማዕከል ስልጠና በመስጠት የመልሶ ማቋቋም ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በዚህም ለስድስት ቀናት የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ በመልሶ ማቋቋሚያ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ይደረጋል ነው ያሉት።

በተሃድሶ ስልጠና የሚያልፉ የቀድሞ ታጣቂዎች የሚሰጣቸው ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም የሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ ለቀጣይ ሕይወታቸው መሰረት የሚያኖር መሆኑንም ገልጸዋል።

በሕዳር 12 ቀን 2017 በመጀመሪያው ምዕራፍ 75 ሺህ የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎችን የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት የመልሶ ማቋቋም ስራ በይፋ መጀመሩን አስታውሶ የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.