Fana: At a Speed of Life!

ሰልፉ ህዝብ ሰላም እንደሚፈልግ ያሳየበት ነው – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ዛሬ የተደረጉ ሰልፎች ህዝቡ ሰላም እንደሚፈልግ ያሳየበት ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ ገለፁ፡፡

ርዕስ መስተዳደሩ በክልሉ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ግጭት በቃን፣ የምንፈልገው ሰላምና ልማት ነው የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈውበታል ብለዋል።

ሰላማዊ ሰልፉ ሕዝባችን ምን ያህል ሰላም እንደሚሻ ያሳየበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ÷ ሰልፎች እንዳይካሄዱ ለማስፈራራት እና ለማሸበር የተደረገው ጥረትም አልተሳካም ነው ያሉት።

በሰልፉ ማህበረሰቡ የታጠቁ ሀይሎች ልዩነታቸውን በውይይት መፍታት እንደሚገባ ያሳሰበ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት በክልሉ ድጋፍ እንደሌለው እና መንግስትን በሀይል እናስወግዳለን የሚለውን ሀይል ያጋለጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ህዝቡ የደገፈው መንግስትን ብቻ ሳይሆን ሰላምን ጭምር ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በሰላማዊ ሰልፉ መንግስት ለሰላም ያደረገውን ጥረት ህዝቡ በአደባባይ የደገፈበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰልፉ በቀጣይ ለሚደረገው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ጉልበት እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ ለሰልፉ ተሳታፊዎችና ለፀጥታ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.