Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአፍሪካን የጋራ ድምፅ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካን የጋራ ድምፅ ለማሳደግ እና የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ቁርጠኛ መሆኗን አስታወቀች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉት የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ኢትዮጵያ ለ2025-2027 የስልጣን ዘመን ለአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት (ኤዩ-ፒኤስ ሲ) አባልነት ዕጩነት ይፋ መሆኗን አስታውቀዋል።

ለዚህም የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራትን ድጋፍ የጠየቁት ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ ለአኅጉሪቱ ሰላም፣ መረጋጋት እና አንድነት ያላትን የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቅኝ ግዛት ነጻ አፍሪካን ዕውን በማድረግ እንዲሁም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ውስጥ ያላትን ቁልፍ ሚና እና በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባልነት መሥራቷንም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የባለብዙ ወገን ትብብርን ለማጠናከር እና የአፍሪካን የጋራ ድምፅ ለማሳደግ በተለይም የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗንም ነው ሚኒስትሩ ያረጋገጡት፡፡

ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና ማጠንጠኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ለአብነትም በሰሜኑ ኢትዮጵያ የነበረውን ግጭት በፕሪቶሪያ ስምምነት በሰላም መቋጨቷን እና የታላቁን ሕዳሴ ግድብን በተመለከተም የሚነሳውን ቅሬታ በአፍሪካ ኅብረት አመቻችነት ለመፍታት መጣሯን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሰላም ማስፈን ተልዕኮዎች እና በግጭት አፈታት ዙሪያ ያላት የካበተ ልምድም ለአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት (ኤዩ-ፒኤስ ሲ) ይጠቅማል ብለዋል፡፡

ለአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የጸጥታ ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማድረግ ያላትን ብቃትም አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ኢትዮጵያ በሰላም ማስፈን ስራዎች የመሪነት አቅሟ በአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ውስጥ ቁልፍ እና ጠቃሚ አባል እንደሚያደርጋት እምነታቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደሮቹ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደታቸው የኢትዮጵያን ታሪክ እና ጠንካራ አቅም ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡም ጠይቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.