ኤኢትሬድ ግሩፕ የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ሊከፍት ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ መገበያያ (ኤኢትሬድ ግሩፕ) የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ለመክፈት የሚያስችለውን ስምምነት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከኤኢትሬድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉዓለም ስዩም ጋር ተፈራርመዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ስምምነቱ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን ተፈጻሚነት ለማፋጠን፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች እና ለዲጂታል ኢኮኖሚው ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።
ተቋሙ የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከፍቶ ወደ ሙሉ ሥራ እንዲገባ መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ኤኢትሬድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉዓለም ስዩም ፥ ተቋሙ በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገልጸው፤ ለኢትዮጵያ እና አፍሪካ ምርቶች ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ተቋሙ የአፍሪካን ንግድ ሥርዓት ዲጂታላይዝድና በኤሌክትሮኒክስ ግብይት የተሳለጠ ለማድረግ በአፍሪካውያን ባለሙያዎች እና የንግዱ ማኀበረሰብ የተመሰረተ መሆኑ ተነግሯል።