በትግራይ ክልል ከ5 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች ማህበረሰቡን ተቀላቀሉ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል 5 ሺህ 728 የቀድሞ ተዋጊዎች በተሃድሶ ስልጠና አልፈው ማህበረሰቡን መቀላቀላቸውን የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን አስታወቀ።
በኮሚሽኑ የፕሮግራም ዕቅድና ክትትል ዳይሬክተር ኮሎኔል በላይ አበበ ፥ በትግራይ ክልል 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን በአራት ወራት ውስጥ በተሃድሶ ስልጠና ወደ ማኅበረሰቡ የመመለስ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በዚህ ሂደትም 5 ሺህ 728 የቀድሞ ተዋጊዎች በመቐለና ዕዳጋ ሐሙስ ማዕከላት በማስገባት የተሃድሶ ስልጠናቸውን አጠናቅቀው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን አስታውቀዋል።
በክልሉ ለቀድሞ ተዋጊዎች የሚሰጠው ስልጠና መደበኛ ህይወታቸውን በሚገባ መምራት በሚያስችል መንገድ መሆኑንም ነው ያብራሩት ዳይሬክተሩ።
በቀጣይም በትግራይ ክልል በዓድዋ ከተማ አካባቢ የሚገኘውን የአዲበራህ የስልጠና ማዕከል የእድሳት ስራ በማጠናቀቅ የተሃድሶ ስልጠና የቅበላ አቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
2ኛ የተሃድሶ ስልጠና በአፋር ክልል 1ሺህ 750 የአፋር ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ አብዓላ ተሃድሶ ስልጠና ማዕከል በማስገባት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተደረሱ የሰላም ስምምነቶች መነሻነትም ለቀድሞ ተዋጊዎች የሚሰጡ የተሃድሶ ስልጠናዎች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል፡፡