Fana: At a Speed of Life!

የመምህራን ምገባ መርሐ-ግብር ዓላማ በትምህርት ጥራት ላይ ለውጥ ማምጣት ነው – ሸገር ከተማ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመምህራን ምገባ መርሐ-ግብር ዋና ዓላማ በትምህርት ጥራት ላይ ለውጥ ማምጣት ነው ሲል የሸገር ከተማ አስተዳደር ገለጸ።

 

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍረኪያ ካሳሁን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት የተለያዩ መርሐ-ግብሮች በመተግበር ላይ ይገኛሉ።

 

ከመርሐ-ግብሮቹ መካከል የተማሪና መምህራን ምገባ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በከተማው በሚገኙ 268 ትምህርት ቤቶች ከ151 ሺህ በላይ ተማሪዎች በምገባ መርሐ-ግብር ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

ከቡኡራ ቦሩ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ባሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ 5 ሺህ 287 መምህራን ምግብ እየቀረበ ነው ብለዋል።

 

መርሐ-ግብሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በመንግስት የተወሰደ አዲስ ርምጃ ነው በማለት ገልጸው፤ የመርሐ-ግብሩ ዋና ዓላማ በትምህርት ጥራት ላይ ለውጥ ማምጣት ነው ብለዋል።

 

ከመምህራን ጥቅማጥቅም ጋር ተያያዥነት የሌለው መሆኑንም አስገንዝበዋል።

 

መምህራን የምገባ መርሐ-ግብሩን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት የምግብ አቅርቦቱ ለትምህርት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ ያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

 

የመማር ማስተማር ሂደቱን በተረጋጋ መንፈስ ለማከናወን እንዳስቻላቸው ጠቅሰው፤ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አኳያ ትልቅ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ ሊጠናከርና ሊስፋፋ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

 

በሲፈን መገረሳ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.