በክልሉ የትምህርት ዘርፍ ማነቆዎችን ለመፍታት የተተገበረው ማሻሻያ ለውጥ እያሳየ መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ዘርፍ ማነቆዎችን ለመፍታት ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ማሻሻያ ለውጥ እያሳየ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
በክልሉ ”የትምህርት ጥራት እምርታ ለሁለንተናዊ ብልጽግና በሚል መሪ ሃሳብ የትምህርት ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡
ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷በትምህርት ዘርፉ በስፋት የሚስተዋለው የጥራት ቸግር ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡
የዘርፉን ችግር በውል በመለየትና በፖሊሲ በመታገዝ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አስረድተዋል።
የት/ቤት ደረጃ ማሻሻያ ንቅናቄ በክልሉ በስኬት መከናወኑን ጠቁመው÷ የመምህራንና የዘርፉን አመራሮች አቅም ግንባታ ሥራ በቀጣይ ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ተናግረዋል።
የመማሪያ መጽሃፍት ተደራሽነት ችግርን ለመቅረፍ ከትምህርት ሚኒስቴር ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በክልሉ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር መቀነስ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው÷በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ የማሟላት ተግባር ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴዔታ አየለች እሸቴ በበኩላቸው÷በዘርፉ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ተደራሽ ማድረግ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የትምህርት ዘርፉ አመራሮችና መምህራን አቅም ግንባታን በመደገፍ ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባ መናገራቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡