Fana: At a Speed of Life!

የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ደህንነት ለማስጠበቅ ያለመ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ/ማ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ደህንነት ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

የፌደራል ፖሊስ ከተሰጠው ተልዕኮ ውስጥ አንዱ የሀገሪቱን መሰረታዊ ተቋማትን መጠበቅ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ፥ ለኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርትም የተሰጠውን ትኩረት በመገንዘብ ራሱን የቻለ መምሪያ በማቋቋም የጥበቃ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል።

ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን አቅም አቀናጅቶ በመጠቀም ውጤታማ የሆነ የጥበቃ ሥራ ለመስራት እንደሚያስችል ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት ÷ የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የሀገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ ዋና መስመርና ከወደብም ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ስምምነቱም በተናጠል ሲሰራ የነበረውን አሰራር በማስቀረት በትብብር ለመስራት የሚያስችል መሆኑን አንስተው ፥ የአገልግሎቱን ደህንነት ለማስጠበቅ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ/ማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ(ኢ/ር) በበኩላቸው ÷ አክሲዮን ማህበሩ ካለበት ኪሳራ ወጥቶ ትርፋማ እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህንን ለማሳካትም ዋነኛ የሆነውን የደህንነት ችግር ለመፍታት ስምምነቱ መደረጉን ገልጸው ፥ ስምምነቱ ተቋሙ በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.