Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰዎች ላይ የጊኒ ዎርም በሽታ አለመከሰቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 7፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) 24ኛው የጊኒ ዎርም በሽታ ማጥፋት ፕሮግራም አፈፃፀም ዓመታዊ ግምገማ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በግምገማ መድረኩ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከጋምቤላ ክልል፣ ከልማት አጋር ድርጅቶች የተውጣጡ አመራሮችና እና ባለሙያዎች እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስታዳደር አቶ ኦሞድ ኡጁሉ፥ ባለፉት ዓመታት የጊኒ ዎርም በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር የተሰሩት ስራዎች በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች ትብብር ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።

በቀጣይም በእርሻ ቦታዎችና በማዕድን ማውጫ ቦታዎች ሰራተኞችና ማህበረሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፥ ባለፉት ሁለት ዓመታት የጊኒ ዎርም በሽታ በሰዎች ላይ አለመከሰቱን አስታውሰዋል።

ይህም ትልቅ የምስራች መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሊያ፥ ስኬቱ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ባለሙያዎች እና ስራው ላይ እየተሳተፉ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች እና ተቋማት ያላሰለሰ ጥረት መሆኑን አውስተዋል።

በሽታውን በዘላቂነት ለማስወገድም ለበሽታው ተጋላጭ መንደሮች ላይ ድመቶችንና ውሾችን በማሰር ጥብቅ ክትትል ማድረግ ፣ ያቆሩ የውሃ ቦታዎችን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ማከም እና የተቀናጀ አሰራርን ማዳበር እንደሚገባና እና ህብረተሰቡም ተሳትፎውን የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የጊኒ ዎርም ማጥፊያ ፕሮግራም የአራት ሀገሮች የበጎ ፈቃድ አምባሳደር የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነ ብርሃን፥የጊኒ ዎርም በሽታን ከሀገራችን ለማጥፋት ለማህበረሰቡ ንጹህ ውሃ እንዲቀርብ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስትና አጋር ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው በዚህ የግምገማ መድረክ በሽታውን በመከላከልና በመቆጣጠር ላይ የተገኙ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የቀጣይ የመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያ ይመከራል ተብሎ ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.