ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ከእስያ-አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጋር መከሩ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከእስያ-አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጂዲ ሲንግህ(ዶ/ር) ጋር ተወያዩ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ውይይቱ በንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ጉዳዮች ዙሪያ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ውይይታችን ትኩረት ያደረገው በኢትዮጵያና በእስያ ንግድ ማህበረሰብ መካከል የሚኖረውን የንግድ ግንኙነት፣ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እና መሰል ጉዳዮች ላይ ነውም ብለዋል።
በዚህም የእስያ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ፣ የእስያ ሀገራት ገበያ ለኢትዮጵያ ምርቶች ይበልጥ ክፍት እንዲሆኑ ምክር ቤታቸው ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ለልዑካኑ እንደገለጹም አብራርተዋል።
በተጨማሪም የልዑካን ቡድን አባላት የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ማሳያ ማዕከልን ጎብኝተዋል።