የግሉ ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ዋና አንቀሳቃሽ እንዲሆን የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት የግሉ ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ዋና አንቀሳቃሽ እንዲሆን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ የብረት ኢንዱስትሪ መንደር የሚገኘውን ስቲሊ አር. ኤም. አይ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የብረታብረት ማምረቻ ፋብሪካን ጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ ፋብሪካው ዘመናዊ የዲጂታል አሠራርን እና የታዳሽ ኃይልን በመጠቀም ከዚህ ቀደም የሚጣሉ የነበሩ የብረት ቁርጥራጮችን መልሶ ጥቅም ላይ እያዋለ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም ለተለያዩ የግንባታ ግብዓት የሚውሉ የብረታብረት ምርቶችን እያመረተ መሆኑ የሚደነቅ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡
የብረታብረት ፋብሪካው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ረገድ አበረታች ውጤቶች እያመጣ እንዳለም ተመልክተናል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት የብድር፣ የመሠረተ ልማትና የአሠራር ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የግሉ ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ዋና አንቀሳቃሽ እንዲሆን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡