Fana: At a Speed of Life!

ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ የወባ መድሃኒቶችን ሲያሰራጩ የተገኙ 156 መድኃኒት ቤቶች ፍቃድ ተሰረዘ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከወባ በሽታ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ ህገ-ወጥ መድሃኒቶችን ሲያሰራጩ የተገኙ 156 መድኃኒት ቤቶች ፍቃዳቸው መሰረዙን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ገለጸ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ የህብረተሰብ ጤናን ለጉዳት የሚዳረጉ ህገ-ወጥ የምግብና መድኃኒት ስርጭትን ለመግታት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለፉት ሦስት ወራት በቅንጅት በተሰራ የቁጥጥር ስራ 59 ሚሊየን ብር የሚገመት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውና የህብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ምግብ ነክ ቁሳቁሶች መወገዳቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም 168 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የህክምና ግብዓቶች እና ደረጃቸውን ያልጠበቁ መድኃኒቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ከወባ በሽታ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ ህገ-ወጥ መድሃኒቶችን ሲያሰራጩ የተገኙ 156 መድኃኒት ቤቶችም ፍቃዳቸው መሰረዙን ገልጸው፤ መድኃኒቶቹም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መወገዳቸውን ዳይሬክተሯ አመላክተዋል።

ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በመውጫና መግቢያ ኬላዎች በተደረገ ቁጥጥርና ፍተሻ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ህጋዊ ሰነድ ያላሟሉ 450 ኩንታል መድኃኒቶች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተገልጿል።

ባለስልጣኑ የምግብ፣ መድኃኒት እና ጤና ግብዓቶች ቁጥጥር ዙሪያ በጅማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመከረ ሲሆን፤ በመድረኩ የህብረተሰብን ጤና ለጉዳት የሚዳረጉ ህገ-ወጥ የምግብ እና መድኃኒት ስርጭትን ለመግታት የቅንጅት ስራ እንደሚያሻም ተመላክቷል።

በወርቃፈራው ያለው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.