የሳዑዲው የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደሚፈልግ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሳዑዲ አረቢያ የማዳበሪያ አምራች የሆነው የንግድ ኢንዱስትሪዎች ኮርፖሬሽን ኩባንያ ከኢትዮጵያ ጋር ቀጥተኛ የሽያጭ መረብ መዘርጋት እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) የተመራ ልኡክ ማዳበሪያ አምራች ከሆነው የሳዑዲ የንግድ ኢንዱስትሪዎች ኮርፖሬሽን ኩባንያ ዋና አስፈጻሚ ፋሃደ አል ባታር ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ ኩባንያው ለኢትዮጵያ ማዳበሪያ ማቅረብ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ እንደነበርም ተገልጿል።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ ያላቸውን ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊካዊና ባህላዊ ቅርበት በመጠቀም የንግድና ኢንቨሰትመንት ትብብር ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት በተሰጠው የግብርና ዘርፍ እየተመዘገበ ስላለው እድገትና ዘርፉ ስለሚፈልገው ሰፊ የማዳበሪያ አቅርቦትም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት ከሳዑዲ ጋር የመንግስት ለመንግስት ስምምነት በመፈፀም ከኩባንያው ማዳበሪያ የመግዛት ፍላጎት እንዳለው አሳውቀዋል፡፡
ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ኩባንያው በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ፋብሪካ እንዲያቋቁምም ጥሪ አቅርበዋል።
የኩባንያው ልኡካን በበኩላቸው አፍሪካ ላይ ምርታቸውን ለመሸጥ ትኩረት እንደሚያደርጉ ገልጸው ፥ በተለይም ኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ የሽያጭ መረብ መዘርጋት እንደሚፈልጉ በአጽንኦት መናገራቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ባለሙያዎች ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።