የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የመረጃና የደኅንነት ተቋማት ትብብራቸውን ለማጠናከር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የመረጃና የደኅንነት ተቋማት የሚያደርጉትን ሁሉን-ዓቀፍ ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል የሚያግዝ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሎችና ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች በደቡብ ሱዳን ኢንተርናል ሴኪዩሪቲ ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል ሌተናል ጀነራል አኬች ቶንግ አሉ ከተመራ የልዑክ ቡድን ጋር በሁሉን-ዓቀፍ የትብበር ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ጠንካራ የሆነ ታሪካዊ፣ ባሕላዊና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ያላቸው ሀገራት እንደሆኑ በምክክሩ የተነሳ ሲሆን÷ የጋራ ዕጣ-ፈንታቸውንና ሕልውናቸውን የሚወስኑ ዘርፈ-ብዙ ትብብሮች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ትስስር ለማረጋገጥ የሚገነባው የመንገድ መሠረተ-ልማት ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑንም አገልግሎቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡
በዚህ ሂደት ከጸጥታና ከደኅንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በመረጃ ልውውጥና በጋራ በሚደረጉ ስምሪቶች መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች መምከራቸውንም አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በድንበር አካባቢ የሚታዩ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ፣ የገንዘብና የሰዎች ዝውውርን ለመግታት እንዲሁም የሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል የሚያደርጓቸውን የትብብር ሥራዎች አጠናክረው በመቀጠል ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማስፈን ይሠራሉ ተብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም የደቡብ ሱዳን የመረጃና ደኅንነት አመራሮችና ባለሙያዎች በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስልጠና መውሰዳቸው የተጠቆመ ሲሆን ÷ በሰው ኃይል ዐቅም ግንባታ ረገድ የሚደረገው ትብብርም ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡
በደቡብ ሱዳን ኢንተርናል ሴኪዩሪቲ ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል የተመሩት የልዑካን ቡድኑ አባላት በአዲስ አበባ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማቶችንና ሌሎችንም ፕሮጀክቶች የጎበኙ ሲሆን ÷ በከተማው የሚታዩት ለውጦችንም አድንቀዋል፡፡
ሌተናል ጀነራል አኬች ቶንግ ከመስከረም 2017 ዓ/ም ጀምሮ በደቡብ ሱዳን ኢንተርናል ሴኪዩሪቲ ቢሮ በዳይሬክተር ጀነራልነት በመሾም ሀገራቸውን እያገለገሉ መሆናቸውንም አገልግሎቱ ጠቁሟል፡፡
በመረጃ፣ በደኅንነትና በጸጥታ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረጉት ትብብሮች ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያድጉ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ተገልጿል፡፡