በጃፓን ድጋፍ የተላላፊ በሽታዎች ሕክምና የልህቀት ማዕከል ሊገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጃፓን መንግስት ድጋፍ የተላላፊ በሽታዎች ሕክምና የልህቀት ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ተፈረመ፡፡
የጃፓን መንግስት በጃይካ (የጃፓን ዓለም-አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ) በኩል በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ማዕከሉ እንደሚገነባም ነው የተገለጸው፡፡
የተላላፊ በሽታዎች ህክምና የልህቀት ማዕከልን በተመለከተ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመና በጃይካ ተወካይ ሚዋ ኢቶ ተፈርሟል።
የልህቀት ማዕከሉ የሚገነባበትን ቦታ ለማዘጋጀትና አስፈላጊውን የህግ ሂደት ለመጨረስ ጤና ሚኒስቴር ከቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር እንደሚሰራም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠቆሙት፡፡
የጃፓን መንግስት የጤና አገልግሎቱን ለማጠናከር እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ ማመስገናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የፕሮጀክቱን አፈፃፀም ዕቅድ በተመለከተ ገለፃ ያደረጉት ሚዋ ኢቶ፥ ፕሮጀክቱ በጃፓንና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ መልካም ግንኙነት እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አብርሃም እሸቱ በበኩላቸው ፥ ሆስፒታሉ ከ60 ዓመት በላይ ተላላፊ በሽታዎችን በማከም ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ሀገር አቀፍ የልህቀት ማዕከሉ ውጤታማ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።