የሕንዱ ተሽከርካሪ አምራች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ተሽከሪካሪ አምራች የሆነው የሕንዱ ሌይላንድ በኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ውስጥ መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍሰሃ ሻወል ከሂንዱጃ ግሩፕ ሊቀመንበር ፕራካሽ ጋር ሲወያዩ ፥ በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ገለፃ አድርገዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያና ምርት ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም አስረድተዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠምና የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ምርት በኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት በፍጥነት እያደጉ ካሉ የመኪና ገበያዎች አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጉን ጨምሮ የፖሊሲ ለውጦች በማድረግ ለውጭ ባለሃብቶች አዳዲስ እድሎችን እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።
ፕራካሽ በበኩላቸው ÷ ከኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ እየሰራ መሆኑን መናገራቸውን በሕንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያ የፖሊሲ ለውጦችን ጨምሮ እያደረገች ያለችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ መሆኑንም ገልፀዋል።