በነዳጅ ሥርጭትና ግብይት የሚስተዋለው ሕገ-ወጥነት…
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ መሠረታዊ የሆነ የነዳጅ አቅርቦት ችግር አለመኖሩን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አረጋገጠ፡፡
አልፎ አልፎ ከሚከሰት የማጓጓዝና ከጅቡቲ ሆራይዘን የነዳጅ ዴፖ የመቅዳት አቅም መቀነስ ጋር ተያይዞ የሚቀንስ የጭነት መጠን ካልሆነ በስተቀር መደበኛ የሆነ የአቅርቦት ችግር አለመኖሩን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡
ሆኖም በአንዳንድ ከተሞች ላይ የሚስተዋሉ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ያለ የሚያስመስሉ ሁኔታዎች በዋነኝነት ከቤንዚን ሕገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚመነጩ ናቸው ብሏል፡፡
የነዳጅ አቅርቦት ችግር ባይኖርም በሥርጭት እና ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች የራሳቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችልም ነው የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በቀለች ኩማ የገለጹት፡፡
በነዳጅ ሥርጭትና ግብይት ላይ የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ ድርጊት ለመቆጣጠርም ነዳጁ ከሚጫንበት ቦቴ እስከ የሚራገፍባቸው ማደያዎች ድረስ በሲስተም የታገዘ ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም እንደወቅቱና ሁኔታዎች ቢለያየም በአማካይ በቀን ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ሚሊየን ሊትር ቤንዚን እና ከ8 ነጥብ 5 እስከ 9 ሚሊየን ሊትር ናፍጣ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ችግር አለመኖሩን ነው ለፋና ዲጂታል ያረጋገጡት፡፡
ምንም እንኳን የነዳጅ አቅርቦት ላይ ችግር ባይኖርም÷ በሥርጭት እና ግብይት ላይ ግን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል፡፡
ይህን ሕገ-ድርጊት በዘላቂነት ለመቅረፍም ከዘርፉ ጋር የተያያዙ አሠራሮችን ሙሉ በሙሉ ከሰው ንክኪ ነጻ በማድረግ በሲስተም እንዲከወኑ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውን ነው ያስታወቁት፡፡
ለአብነትም ነዳጁ ከሚጫንበት ጂቡቲ ጀምሮ እስከሚራገፍባቸው ማደያዎች ድረስ በሲስተም የታገዘ ሥራ በትጋት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ችግሮች እየታዩ ያሉትም ነዳጁ ከተራገፈ በኋላ በሚኖሩ የሥርጭትና ግብይት ሂደት ላይ መሆኑን በማስገንዘብ÷ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ የተወሰኑ ማደያዎች ላይ ለሦስት ወራት የሚቆይ ዕግድ ተላልፏል ብለዋል፡፡
የማጓጓዝ ሥራውን በሲስተም በመቆጣጠር አበረታች ውጤት መገኘቱን ተከትሎ በሥርጭትና ግብይት ያለውን ሂደት የሚቆጣጠር ሲስተም በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት ማደያዎች ላይ በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከዘርፉ ጋር በተያያዘ በሕገ-ወጥ ድርጊት ተሳትፈው የተገኙ ሰዎችን በበቂ መጠን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል የነዳጅ አቅርቦት እና ግብይት ቁጥጥር አዋጅ ለማውጣት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሂደት ላይ ነው ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው