በሰላም ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰላምና በአንድነት ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
ሁሉም ሰው የያዘውን ልዩነት ይዞ እርስበርስ ተከባብሮ መኖር የትክክለኛ ሰውነት መገለጫ መሆኑን የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ አስገንዝበዋል፡፡
አሁን ያጋጠሙ ሀገራዊችግሮችን የምንፈታበት ሂደት ለቀጣይ ሰላም ግንባታ ልምድ የሚወሰድበት ነው ብለዋል፡፡
ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው ሁሉም ሰው እንደ እኔ ያስብ ብሎ ማስገደድ አይቻልም ያሉት ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ÷ ልዩነትን አክብሮ መኖር ግን የትክክለኛ ሰውነት መገለጫ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በጉባዔው የሁሉም ሐይማኖት ተቋማት የሐይማኖት አባቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
ጉባዔው ሐይማኖቶች ለሰላም፣ ለአንድነት እና አብሮ ለመኖር እንዲሁም ለሀገር ግንባታ በሚል መሪ ሐሳብ ነው እየተካሄደ ያለው፡፡
በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ የሰላም መደፍረሶችን መቅረፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጉባዔው ግንዛቤ እንደሚሰጥ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
ሰላሟ የተጠበቀ ሀገር ለቀጣይ ትውልድ ለማስረከብ የሐይማኖት አባቶች ሚና ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሜሮን ሙሉጌታ እና ኦብሴ ዋቅጋሪ