በኦሮሚያ ክልል ከ800 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጠረ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አምስት ወራት ከ800 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን የክልሉ የሥራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቶለሳ አጀማ እንደገለጹት÷ በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በዚህም ባለፉት አምስት ወራት በተደረገ እንቅስቃሴ ለ886 ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል መፈጠሩን ነው የተናገሩት፡፡
የሥራ እድሎቹ የተፈጠሩት ክልሉ በተለይም በግብርናና እንስሳት እርባታ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ያለውን ትልቅ አቅም መሰረት በማድረግ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ክልሉ ያለውን ሰፊ የመልማት አቅም በመጠቀም የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው 886 ሺህ ዜጎች መካከል 52 በመቶዎቹ በግብርናና በእንስሳት እርባታ መሰማራታቸውን አብራርተዋል፡፡
ቢሮው እቅዱን ለማሳካት የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት በስራ እድል ፈጠራ፣ በስልጠና፣ ጥራትና ብቃት ማረጋጋጥ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ልማት ላይ ሰፊ ሥራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
በክልሉ ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች አጫጭር ስልጠናዎችን ለመስጠትና የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሳካ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በብድር መቅረቡን ገልጸዋል።
በክልሉ በተለያዩ ከተሞችና ዞኖች ለተደራጁ ኢንተርፐራይዞች 25 ሺህ 695 ሄክታር መሬት ማምረቻና መሸጫ ቦታዎችን ማቅረቡን ለኢዜአ ተናግረዋል።