የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በዓሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በአርባምንጭ ከተማ በድምቀት ተከብሮ እና የታለመለትን ዓላማ አሳክቶ መጠናቀቁንም አቶ አገኘሁ ገልጸዋል፡፡
በዓሉ የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ኅብረብሔራዊ አንድነትና የሕዝቦችን ትስስር በሚያጠናክር መልኩ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት መከበሩንም አስታውሰዋል፡፡
የአዘጋጁ የደቡብ ኢትዮጵያን ክልል ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፀጋዎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ቦታዎች፣ መኅበራዊና ባህላዊ ሃብቶችን በስፋት ማስተዋወቅ እንደተቻለም መግለጻቸውን ከምክርቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አቶ አገኘሁ ተሻገር በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለደቡብ ክልል መንግሥትና ሕዝብ፣ ለሁሉም የፀጥታና ደኅንነት አካላትና ለሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል::