ኢትዮ ኢንጂነሪንግና ጁክሮቫ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ቴክኖሎጂ አቅርቦት ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እና የቱርኩ ጁክሮቫ ኩባንያ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ቴክኖሎጂ አቅርቦት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና የጁኩሮቫ ኩባንያ ጀነራል ማናጀር ሙስተፋ ያፒሲ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ክራውለር ኤክስካቫተር፣ ዊል ሎደርና ባክሆ ሎደር ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ሙሉ ቴክኖሎጂ ለማቅረብ ያስችላል ተብሏል።
በኮንትራት ስምምነቱ ውስጥ የቴክኖሎጂውን ትግበራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጀመር እንዲቻል 30 ማሽኖችና መለዋወጫዎች በሲኬዲና በኤስ ኬዲ እንደሚገቡ ተገልጿል።
ይህም የቴክኖሎጂውን ሽግግር ለማሳለጥ የሚያስችል ሲሆን፥በሒደት በሎካላይዜሽንና ጆይንት ኢንጂነሪንግ ምርቱን በሀገር ውስጥ ለማምረት እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።
ቴክኖሎጂን ማስተላለፍ የሚያስችሉ የዲዛይን፣ የሰፕላይ ቼይን፣ የምርምርና ልማት፣ የግብይትና ሽያጭ፣ የጥራት ቁጥጥርና ማረጋገጫ ተከታታይ ስልጠናዎች እንደሚሰጡም የኢትዮ ኢንጂነሪንግ መረጃ ያመላክታል።