የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በኤርትራ ከረን ደማቅ አቀባበል ተደረገለት
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 7 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ60 በላይ አባላትን የያዘው የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በኤርትራ ከረን ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ቲያትር፣ ከታዋቂ ደምጻውያንና የጃኖ ባንድ ሙዚቀኞችን ያካተተው የኢትዮጵያ ባህል ቡድን በትናንትናው ዕለት ኤርትራ አስመራ መግባቱ ይታወሳል።
የባህል ቡድኑ በዛሬው ዕለት ከረን ከተማ ሲገባም ደማቅ አቀባበል የተደረገለት መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የባህል በድኑ ጉዞ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተፈጠረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው።
ቡድኑ ለአንድ ሳምንት በኤርትራ የሚቆይ ሲሆን፥ ከከረን በተጨማሪ በምፅዋ ከተማ የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።