Fana: At a Speed of Life!

 ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በጅማ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ስራ ሊጀምሩ ነዉ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በጅማ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በቡና እና በሻይ ቅጠል ምርት ስራ ሊጀምሩ ነዉ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) እና የጅማ ዞን ዋና አስተዳደር ቲጃኒ ናስር በጅማ ዞን ማና ወረዳ በክላስተር እየለሙ ያሉ የቡናና ሻይ እርሻዎችን፤ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎችን ተመልክተዋል።

ዶ/ር ፍሰሃ በወቅቱ እንዳሉት፤ ቡናን ፕሮሰስ በማድረግ ለዉጭ ገበያ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ለመግባት በሂደት ላይ ናቸው።

ይህም በጅማና አካባቢዋ ለሚገኘዉ አርሶአደር ዘላቂ የገበያ ትስስር የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

የኩባንያዎቹ ወደ ስራ መግባት በጅማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የኢንቨስትመንት መነቃቃት እንደሚፈጥር እና ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶች ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

የጅማ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በቡናና ሻይ ልማት ለተሰማሩ የአካባቢው አርሶአደሮች ትልቅ ፀጋ መሆኑን ጠቅሰው፤ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ከአቮካዶ ፍሬ ዘይት በማምረት ለአሜሪካ ገበያ የሚያቀርበው አክሻይ ጄ ኩባንያ ለዚህ ማሳያ ነዉ ብለዋል።

ኩባንያው ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በቡናና ሻይ ምርት ባለሃብቶች በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ እንዲሰማሩ በኮርፖሬሽኑ በኩል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረው፤ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

ቡናና ሻይ ቅጠልን በማቀነባበር ሙሉ በሙሉ ለዉጭ ገበያ የሚያቀርቡት ኩባንያዎቹ ወደ ስራ ሲገቡ ከ2 ሺህ በላይ ዘላቂ የስራ ዕድል እንደሚፈጠር የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.