ስለሺ ስህን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አትሌት ስለሺ ስህን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ።
አትሌት ስለሽ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባካሄደው 28ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው ለቀጣይ አራት አመት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን በመተካት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የተመረጠው፡፡
አትሌት ስለሺ በመካከለኛ ርቀት 3 ሺህ ሜትር፤ በረጅም ርቀት 5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር፤ በ10፣ 15 እና 20 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫዎች፤ በሀገር አቋራጭ፤ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን ውድድሮች ከ15 ዓመታት በላይ ተወዳድሯል፡፡
አትሌት ስለሺ ከእነ አበበ ቢቂላ፤ ማሞ ወልዴና ምሩፅ ይፍጠር በኋላ በዓለም አትሌቲክስ ፍፁም የበላይነት የነበረው የአረንጓዴው ጎርፍ ትውልድን ከነ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ጋር በመሆን ገንብቷል፡፡
ውድድር ከተወበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ሀላፊነቶች ሲያገለገል የነበረው አትሌት ስለሺ ስህን፤ በቀጣይም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ለአራት አመታት በፕሬዚዳንትነት የሚመራ ይሆናል፡፡
አትሌቱ ካለው የረጀም ጊዜ የአትሌቲክስ ውድድር ልምድ እና ግለሰባዊ ስነ-ምግባር ጋር አንፃር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያጋጠመውን ስብራት በመጠገን ወደ ቀድሞው ገናናቱ ይመልሰዋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡