የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት አካል የሆኑ የዲጂታል አገልግሎቶች ሥራ ጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት አካል የሆኑና የሥራ ሥነ-ምህዳሩን ያሰፋሉ የተባሉ ሁለት የዲጂታል አገልግሎቶችን ሥራ አስጀምረዋል፡፡
ሚኒስትሯ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ አገልግሎት የጀመሩት ብሔራዊ የሥራ ፖርታል እና የሀሳብና ክህሎት ባንክ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ወደ ሥራ የገባው ብሔራዊ የሥራ ፖርታል ዜጎች የሀገር ውስጥ፣ የውጪ ሀገር እና የሪሞት የሥራ ዕድሎችን በአንድ ቦታ በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያግዝ ስርዓት ነው ብለዋል፡፡
የሀሳብና ክህሎት ባንኩ ደግሞ የፈጠራ ሀሳብ እና ክህሎት ያላቸው ዜጎች ሀሳብና ክህሎታቸውን የሚያካፍሉበት፣ ለገበያ የሚያቀርቡበት እንዲሁም ሀሳብና ክህሎታቸውን አቅናጅተው ሥራ የሚፈጥሩበትን ትስስር መፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ይህም የሥራ ፈጠራ ስነ-ምህዳሩን ምቹ፣ ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ቀላጣፋ ማድረግ እንደሚያስችል በመግለጽ እንደ ሀገር የተቀረፀውን የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ አዉን የማድረጉ ሂደት ላይ ተጨማሪ እሴት አካይ ተግባር ነው ብለዋል፡፡