አሜሪካ ለታይዋን የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ በእሳት እንደመጫወት ነው – ቻይና
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ ለታይዋን የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ “በእሳት እንደመጫወት ነው” ስትል ከድርጊቷ እንዲትቆጠብ ቻይና አስጠነቀቀች።
ቻይና ይህንን ያለችው አሜሪካ ለታይዋን 571 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ እና 295 ሚሊየን ዶላር የሚገመት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማጽደቋን ተከትሎ ነው።
የቻይና መንግስት አሜሪካ ለታይዋን የምትሸጠው የጦር መሳሪያ የአንድ ቻይናን መርህ እና ሦስቱን የቻይና እና የአሜሪካ የጋራ ስምምነቶችን የጣሰ ነው በማለት ወቅሷል።
በቻይና የመንግስት ምክር ቤት የታይዋን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ዡ ፌንግሊያን ታይዋን የጦር መሳሪያ በማቅረብ ነፃነቷን እንድታገኝ መርዳት አደገኛ እና አሜሪካ ላይም ምላሽ የሚያሰጥ ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ታይዋንን የማስታጠቅ ድርጊት በአካባቢው አለመረጋጋት አየፈጠረ መሆኑን ገልፀው እነዚህን ርምጃዎች በአስቸኳይ እንድታቆም ማስጠንቀቃቸውን ዢንዋ ዘግቧል፡፡
ቤጂንግ ብሄራዊ ደህንነቷን እና የግዛቷን አንድነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ ርምጃ እንደምትወስድም ነው የተናገሩት፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አሜሪካ ለታይዋን የ385 ሚሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማጽደቋ የሚታወስ ነው።