Fana: At a Speed of Life!

ለልማት በሚል ገንዘብ ሰብስበው ለግል ጥቅም ያዋሉ በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሸገር ከተማ አስተዳደር ለልማት በሚል ከማህበረሰቡ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ በመሰብሰብ ለግል ጥቅም በማዋል የተከሰሱ በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ወሰነ።

የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሸገር ከተማ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ዐቃቤ ሕግ 1ኛ በሸገር ከተማ በሱሉልታ ክፍለ ከተማ የወሰርቢ ወረዳ አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሲፈሌቴ ከበደ፣ 2ኛ የወረዳው የፋይናን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሸብር ኦልጅራ፣ 3ኛ የማዘጋጃ ቤት ኃላፊ ጉታ ኤጀሬ እና የወረዳው የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ገመቹ ማሞ የተባሉ አመራሮች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ጠቅሶ ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በዚህ ባቀረበው ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ ከሸገር ከተማ አስተዳደርም ሆነ ከክፍለ ከተማው ፍቃድ ሳይሰጣቸው በ2016 ዓ.ም በሱሉልታ ክፍለ ከተማ ወሰርቢ ወረዳ ከተለያዩ ባለሃብቶች እና ከሌሎች የማህበረሰቡ ክፍል ለልማት በሚል በህገ ወጥ መንገድ በራሳቸው ስም በከፈቱት የባንክ ሂሳብ 3 ሚሊየን 80 ሺህ ብር ሰብስበው ገንዘቡን ከባንክ አውጥተው ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርባባቸው ነበር፡፡

በዚህ መልኩ የቀረበባቸው ክስ ዝርዝርን 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸውና ክሱን በንባብ እንዲሰሙ ተደርጎ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃል በመስጠታቸው ዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክር ቃልና የሰነድ ማስረጃን አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል ባለመቻላቸው ባሳለፍነው ሳምንት የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል።

ቀደም ሲል ሸሽታ ሳትያዝ የቀረችው የወረዳው አስተዳዳሪ ነበረች የተባለችው ሲፈሌቴ ከበደ በቁጥጥር ስር ውላ ችሎት ቀርባ የነበረ ሲሆን÷ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ለጊዜው በቁጥጥር ስር እስክትውል በፍርድ ቤቱ የተቋረጠው የተከሳሿ ጉዳይ ተነጥሎ እንዲቀጥል በችሎት ጠይቆተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ ያስተላለፈባቸውን 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ያቀረቡትን የቅጣት አስተያየት በመያዝ እያንዳንዳቸውን በ5 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራትና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.