Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አጋርነት እያደገ መጥቷል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልፅግና ፓርቲ እና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አጋርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይታቸውም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት፣ የሁለቱ ሀገራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት ዙሪያ መክረዋል፡፡

በዚሁ ወቅት አቶ አደም ፋራህ÷ የኢትዮ-ቻይና ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልፅግና ፓርቲ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝና የቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ አጋርነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደመጣ አንስተዋል።

ከዚህ በፊት በሁለቱ ፓርቲዎች ስምምነት መሰረት በስልጠና እና ልምድ ልውውጥ አብሮ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት መደረጉን አስታውሰዋል።

በቅርቡ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት የልኡካን ቡድን ቆይታ የስምምነቱ ፍሬያማነት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቶች በስልጠና እና በልምድ ልውውጥ መርኃ ግብሮች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልፅግና ፓርቲ ፍላጎት እንዳለው መግለጻቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ቸን ሃይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቻይና ጠንካራ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው÷ ግንኙነቱ በፓርቲ ለፓርቲም ሆነ በመንግስታዊ ወዳጅነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ መንግስታቸው አበክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የአንካራ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥም አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.