ኮርፖሬሽኑ የፉጃን ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሰራ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፉጃን ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሰራ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ከቻይና ፉጃን ግዛት ከመጡ ከፍተኛ የመንግስት ልዑካን ጋር ባደረጉት ውይይት÷የፉጃን ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የድጋፍና ክትትል ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ባለሃብቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የማምረቻ ሼዶችንና የለማ መሬት ከተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ጋር ማዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሀብታቸውን እና እውቀታቸውን ስራ ላይ ለማዋል ለሚወስኑ የግዛቷ ባለሀብቶች ስኬታማነት ኮርፖሬሽኑ ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
የፉጃን ግዛት የፖለቲካ ቆንስላ ምክትል ሊቀመንበር እና የልዑካን ቡድኑ መሪ ሁዋንግ ዌንሁይ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የውጭ ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያከናወነቻቸው የማሻሻያ ስራዎች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እንዲሸጋገሩ ማድረጓ ለፉጃን ባለሃብቶች መልካም እድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የፉጃን ባለሃብቶች በግብርና ፣በቴክስታይል፣ በኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠም ዘርፍ እና በሌሎችም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ያካበቱት ልምድ ስራ ላይ እንዲያውሉ ያስችላል ብለዋል፡፡