የአዋሽ ኮምቦልቻ የባቡር ፕሮጀክትን ከዘረፋ መጠበቅ እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዋሽ ኮምቦልቻ – ወልዲያ ሃራገበያ ፕሮጀክት ከውድመትና ከዘረፋ ለመጠበቅ ትኩረት ስጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አሳሰበ።
በፕሮጀክቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ውድመት ለመከላከል የባቡር መሰረተ ልማቱ ከሚያልፍባቸው የአማራና አፋር ክልላዊ መንግሥት መስተዳድሮች፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ኮርፖሬሽኑ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዲሁም የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የአማራ እና የአፋር ክልል አመራሮች በተገኙበት በተካሄደ ውይይት የኘሮጀክቱን ንብረት በሚሊሽያ ጽ/ቤት በኩል ለማስጠበቅ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲሆን በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የጥበቃ ሥራውን ለማከናወን ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡
መሠረተ ልማቱ የሚያልፍባቸው አካባቢዎች ፕሮጀክቱን ከውድመትና ከዘረፋ ለመጠበቅ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸውም ኮርፖሬሽኑ አሳስቧል፡፡
በክልሎች በኩል ህብረተሰቡን በማስተባበር በንብረቱ ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ዘራፊዎችና ተቀባዮች ላይ ህጋዊ ርምጃ እየተወሰደ እና በኤግዚቢትነት የተያዙ ንብረቶች የማስመለስ ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑም ተመላክቷል፡፡