የፍርድ ውሳኔን በመሻር ታራሚ እንዲፈታ ትዕዛዝ የሰጡ ዳኞች በእስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔን በመሻር ከስልጣናቸው ውጪ ታራሚ እንዲፈታ ትዕዛዝ የሰጡ ዳኞች በ1 ዓመት እስራት እንዲቀጡ የጋምቤላ ከተማ አካባቢው ከፍተኛ ፍ/ቤት ወንጀል ችሎት ወሰነ።
ተከሳሾቹ 1ኛ የአኘዋሃ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዳንትና ዳኛ አቡላ ሚዶ፣ 2ኛ ተከሳሽ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ዳኛ አገቱ ኤጋላ፣ 3ኛ ተከሳሽ የዞኑ ማረሚያ ቤት የደህንነትና መሠረታዊ ፍላጎት ምክትል አዛዥ ኢንስፔክተር ኡስማን አቶዋሉ ናቸው።
የጋምቤላ ክልል ፍትህ ቢሮ ዐቃቤ ሕግ በአንደኛው ክስ ዝርዝር ላይ በ1ኛ እና በ2ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር (1) ሀ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ በስልጣን ያለአግባብ መገልገል የሚል ሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
በዚህ በቀረበ ክስ ላይ እንደተመላከተው 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የአኝዋሃ ብሔረሰብ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት አበኪዬው ኡጃሃ የተባለ ግለሰብ በተከሰሰበት አደንዛዥ ዕፅ ማዘዋወር ወንጀል በጋምቤላ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ፈጣን ችሎት የተጣለበትን የ7 ዓመት ፅኑ እስራት ተከሳሹ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሶ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ የጠየቀ መሆኑ በክስ ዝርዝር ላይ ተጠቅሷል።
ይግባኙን የተመለከተው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ሆነ የሰበር ሰሚ ችሎት እስራቱ ተሻሽሎ ከ7 ዓመት ወደ 5 ዓመት በማውረድ በእስራት እንዲቀጣ በመወሰን እና እስራቱን ከጋምቤላ ከተማ ማረሚያ ቤት ወደ አኝዋሃ ዞን ማረሚያ ቤት ተዛውሮ እንዲፈፅም ይፈቀድለታል።
ከዚህ በኋላ ታራሚው “በጋምቤላ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤትም ሆነ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተወሰነብኝ ቅጣት የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኔን ግምት ውስጥ ያላስገባ ስለሆነ እንደገና እንዲታይልኝ ” በሚል በነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ለአኝዋሃ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ጽፎ ያቀረበውን የማመልከቻ አቤቱታ በመቀበል ከስልጣናቸው ውጪ በመዝገብ ቁጥር 04065 አቤቱታው በቀረበበት በዛው ዕለት በዋለው ችሎት ተከሳሾቹ የጠቅላይ ፍርድ ቤትንም ሆነ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔን በመሻር ታራሚው የተወሰነበትን ገንዘብ ለመንግስት የከፈለ ስለሆነ ከእስር እንዲፈታ የሚል ውሳኔ በመወሰን ትዕዛዝ በመስጠት ታራሚው ከማረሚያ እንዲፈታ ማድረጋቸው ተጠቅሶ የጠቅላይ ፍ/ቤትን የመጨረሻ ውሳኔ የመሻርም ሆነ ጉዳዩን እንደገና የማየት ስልጣን ሳይኖራቸው የፈፀሙት ተግባር በመሆኑ በስልጣን ያለአግባብ መገልገል ሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ሁለተኛው ክስ ደግሞ በ3ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን ይኸውም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 10 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ 3ኛ ተከሳሽ የአኝዋሃ ዞን ማረሚያ ቤት ም/አዛዥ ሆኖ በሚሰራበት ወቅት በ1ኛ ክስ ላን የተጠቀሰውን ክስ ጉዳይ ማስፈፀሚያ ከታራሚው ባለቤት የተላከ ገንዘብ ብር 60 ሺህ ብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አበቦ ቅርንጫፍ በስሙ በተከፈተ ሂሳብ ወጪ በማድረግ ለ2ኛ ተከሳሽ መስጠቱ ተጠቅሶ ጉቦ ማቀበል ሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡
ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ከክስ ዝርዝሩ ጋር የሰውና የሰነድ የማስረጃ ዝርዝር አያይዞ በማቅረቡ ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ ከደረሳቸው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን መፈጸማቸው አምነው ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮና ተከሳሾቹ አምነው ቃላቸውን መስጠታቸውን ከግምት በማስገባትና ያቀረቡትን የቅጣት አስተያየት በመያዝ እያንዳንዳቸውን በአንድ ዓመት እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ