በትራፊክ አደጋ ነፍሰጡር እናትን ጨምሮ የ4 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዋጫሌ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ለመውለድ ወደ ሆስፒታል በአምቡላንስ ስተወሰድ የነበረች ነፍሰጡር እናትን ጨምሮ የአራት ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡
አደጋው ከሙከ ጡሪ ወደ አዲስ አበባ ሪፈር የተባለች ወላድ እናት እና ቤተሰቦቿን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አምቡላንስ ዱበር ከተሰኘ ድልድይ ላይ በኤፍ ኤስ አር የጭነት ተሽከርካሪ ከኋላ ተገጭቶ ወደ ድልድዩ በመውደቁ ነው ተብሏል፡፡
በደረሰው አደጋም ነፍሰጡር እናትን ጨምሮ የነፍሰጡሯ ወላጅ እናት እና ባለቤት እንዲሁም የአምቡላንሱ አሽከርካሪ ሕይወት ማለፉ ተገልጿል፡፡
የአደጋው መንስኤ የኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪው ፍሬን መበጠስ መሆኑን የዋጫሌ ወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት የመረጃ ክፍል ባለሞያ ሳጅን አብዶ አሊይ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡