Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ጸረ-ሰላም ኃይሎችን ለመግታት የጋራ ግብረ-ኃይል አቋቁመው ለመሥራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያና የጅቡቲ ደኅንነት ተቋማት በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ጸረ-ሰላም ኃይሎችን ለመግታት የጋራ ግብረ-ኃይል አቋቁመው ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

ሀገራቱ በድንበሮቻቸው አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ጸረ-ሰላም ኃይሎችን ለመግታት ከሚያደርጉት የመረጃ ልውውጥ ባሻገር የጋራ ግብረ-ኃይል አቋቁመው ስምሪት ለማከናወንና ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት ነው የተስማሙት፡፡

በጅቡቲ ሪፐብሊክ የሴኪዩሪቲ ዶክመንቴሽን ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ሐሰን ሰይድ ካይራ የተመራ ልዑክ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

የአገልግሎቱ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንና የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በጅቡቲ ሪፐብሊክ የሴኪዩሪቲ ዶክመንቴሽን ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ሐሰን ሰይድ ካይራ ከተመራው ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በጸጥታ፣በደኅንነትና በተያያዥ መስኮች ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት የጋራ ስጋቶች መመከት የሚያስችሉ እንዲሁም ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማምጣት የሚረዱ ጉዳዮች ዋንኛ የምክክሩ አጀንዳዎች እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡

ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተለይም ሕገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመግታትና ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ለመከላከል የሚደረገውን ትብብር ለማጠናከር መስማማታቸውም ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ በኩል የምታከናውነው የወጪ ገቢ ንግድ ላይ የሚስተዋሉ የደኅንነት ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ውይይት መካሄዱንም አገልግሎቱ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.