የሚወጡ ሕጎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ይሆኑ ዘንድ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል- አፈ-ጉበዔ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚወጡ ሕጎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ይሆኑ ዘንድ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉበዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተባባሪ ኮሚቴ የምክር ቤቱን የ2017 በጀት የሩብ ዓመት አፈፃፀም ገምግሟል፡፡
በመድረኩ አፈ-ጉበዔ ታገሰ ጫፎ÷ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴዎቹ እና በተለያዩ አደረጃጀቶች እየተከናወኑ ያሉት ስራዎች በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ የሚያወጣቸው ህጎች የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ተፈጻሚነት ይኖራቸው ዘንድ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚኖርበት አብራርተዋል፡፡
ቀደም ሲል የጸደቁት ህጎችም መታረም ካለባቸው በድጋሚ መታየት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉበዔ ሎሚ በዶ በበኩላቸው÷ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ በተሻለ ቅንጅት በመስራቱ በህግ አወጣጥ፣ በክትትልና ቁጥጥር፣ በህዝብ ውክልና እንዲሁም በፓርላማ ዲፕሎማሲረገድ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
የምክር ቤቱን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ የሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት በዝርዝር ያቀረቡት ደግሞ÷የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ምስራቅ መኮንን (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ቋሚ ኮሚቴዎች በህግ አወጣጥ፣ በክትትልና ቁጥጥር ረገድ እንዲሁም በህዝብ ውክልና ሥራ፣ በፓርላማ ዲፕሎማሲ እና በአቅም ግንባታ በሩብ ዓመቱ ያከናወናቸውን ተግባራት አብራርተዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ 5 ህጎች እንደጸደቁ በመግለጽ 23 ረቂቅ ህጎች በሂደት ላይ ናቸው ማለታቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡