በኦሮሚያ ክልል ከ1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ተጠገነ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከ1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ መጠገኑን የኦሮሚያ ክልል መንገዶች እና ሎጂስቲክስ ቢሮ አስታወቀ፡፡
በ2017 የበጀት ዓመት ከ13 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገዶችን ለመጠገን እየተሠራ መሆኑን የቢሮው ምክትል፣ የመንገዶች ጥገና እና ንብረት አሥተዳደር ኃላፊ ሞሐመድ ኑራ (ኢ/ር) ለፋና ዲጅታል ተናግረዋል፡፡
ከጥራት ጋር በተያያዘ ማሕበረሰቡ የሚያነሳባቸውን ቅሬታቸው ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የጠጠር መንገድ ጥገና ሥራ የሚከናወነው ከፌደራል መንግሥት በተመደበ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን እና በወረዳዎች በሚሸፈን 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እንዲሁም በክልሉ የመንገድ ፈንድ ድጋፍ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአጠቃላይ የክልሉ የመንገድ ሽፋንም ከ61 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መድረሱን ነው ያስረዱት፡፡
በፀሐይ ጉሉማ