በክልሉ የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ምርት ላይ አሉታዊ ጫና ማስከተሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ምርት ላይ አሉታዊ ጫና ማስከተሉን የክልሉ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተርና የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማትና ጥበቃ ዘርፍ ኅላፊ አቶ በላይ ኮጁአብ ለፋና ዲጂታል እንደተናገሩት፤ የዘንድሮ የቡና ምርት ከአምናው አንጻር ሲታይ ቅናሽ ታይቶበታል።
በክልሉ ለታየው የምርት መቀነስ የአየር ንብረት ለውጡ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በቡና አምራች አካባቢዎች ዝናብ አለመቋረጡን ገልጸው፤ ይህ ደግሞ በባህሪው ቢያንስ 2 ወራት በፀሐይ መመታት ለሚፈልገው የቡና ተክል አሉታዊ ጫና መሆኑን አመልክተዋል።
ዝናብ መብዛቱ እና ያበበው ቡና የመርገፍ ሁኔታ በማሳየቱም የምርት መቀነስ መከሰቱን ተናግረዋል።
አምና ከ300 ሺህ ቶን በላይ ቡና መመረቱን ያስታወሱት አቶ በላይ፤ የዘንድሮው የምርት ትመና የሚያሳየው 270 ሺህ ቶን መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ 67 ሺህ ቶን ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለመላክ እና ቀሪውን ለአካባቢው ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ገልፀው፤ እስካሁንም 20 ሺህ ቶን ምርት ተሰብስቦ መጋዘን መግባቱን አመልክተዋል።
በክልሉ በስድስቱም ዞኖች የቡና ተክል እየለማ ሲሆን÷ ቤንች ሸኮ፣ ካፋ እና ሸካ ዞኖች ከፍተኛ ሽፋኑን ይይዛሉ፡፡
በፌቨን ቢሻው