ምክር ቤቱ 12ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 12ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው፡፡
በስብሰባውም የአረንጓዴ ዐሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያ እና አሥተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡
ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶም የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ ለምክር ቤቱ ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ረቂቅ አዋጁን በጥልቀት መመርመሩን እና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋርም የሕዝብ ውይይት ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
የተጎሳቆለ መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ደኖችን በመጠበቅና በመንከባከብ ለኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና የሥነ-ምኅዳር ጥቅም እንዲሰጥ በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም ለአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች ቋሚና ተቋማዊ ሥርዓት ያለው የፋይናንስ አቅም እንዲኖር ማስቻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን ነው ያብራሩት፡፡
እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋምና ከአየር ንብረት ብክለት የፀዳ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተያዘውን ሀገራዊ ራዕይ እንዲሳካ አስተዋጽኦ ለማድረግ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ዛሬ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡
በየሻምበል ምኅረት