Fana: At a Speed of Life!

የአረንጓዴ ዐሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አሥተዳደር አዋጅ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በደን ዘርፍ ከልማት አጋሮች የምታገኘውን ድጋፍና ጥቅም ለማሳደግ የሚያስችል የአረንጓዴ ዐሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አሥተዳደር አዋጅ ፀደቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባ÷ የአረንጓዴ ዐሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያ እና አሥተዳደር አዋጅን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት አዋጁን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት÷ ዘላቂ ፈንድ ከማቋቋም አንጻርና ችግሩን ለመፍታት የተደረገው ጥረት ጥሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሀገር ውስጥን አቅም አሟጥጦ ለመጠቀምና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአየር ንብረት ለውጥ የሚደረጉ ድጋፎችን ለማግኘት የሚያስችል አዋጅ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የራሱ በጀት እንዳልነበረው አውስተው÷ በቀጣይ ራሱን ችሎ በልዩ ፈንድ ተደግፎ እንዲቀጥል የሚረዳና በርካታ ሥራዎችም በአዋጁ ውጤታማ እንደሚሆኑ አመላክተዋል፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ ለተተከሉና የሚተከሉ ችግኞች ቀጣይነት ባለው መልኩ በተቀናጀ አግባብ መንግሥት የበጀት ድጋፍ እንዲያደርግ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በደን ዘርፍ ከልማት አጋሮች እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ሰጪ ምንጮችና ከካርበን ግብይት ሥርዓቶች የምታገኘውን ድጋፍና ጥቅም ለማሳደግ እንደሚረዳም ነው የተገለጸው፡፡

በየሻምበል ምኅረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.