Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎችን ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎችን ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

“ጤናችን በእጃችን” በሚል በሮሃ እና ዳልበርግ ግሩፕ በተባሉ ድርጅቶች አነሳሽነት በመንግስት እና በግል ዘርፍ እንዲሁም በግብረሰናይ ድርጅቶች የጋራ ትብብር ለቀጣይ 6 ወራት የሚቆይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት ይፋ ሆኗል።

የድጋፍ ፕሮጅክቱን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ እና የሮሃ አፍሪካ ዳይሬክተር ወለላ ሃይለስላሴ በጋራ አስጀምረዋል፡፡

“ጤናችን በእጃችን” በሚለው ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከል ፕሮጀክት ተግባራዊ የሚደረገው በቅርቡ ይፋ በሆነው መንደርን መሰረት ያደረገ የብሎክ አደረጃጀት አማካኝነት መሆኑንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክረተሪ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

በዚህም 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎችን ቀጥታ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ይደረግላቸዋል ተብሏል።

በተጨማሪም ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ላይ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደሚሰሩ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የጋራ ቅንጅት በ6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚተገበር መሆኑንም ታውቋል።

የፕሮጀክቱ የሙከራ ጊዜ የሚያስፈልገውን 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በሮሃ ግሩፕ በኩል የተገኘ ሲሆን፥ ቀሪው 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ከለጋሽ ድርጅቶች የግሉ ዘርፍ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንደሚሰበሰብ ተገልጿል።

የሚሰበሰበው ገንዘብም በአዲስ አበባ ከተማ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለተለዩ አካባቢዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶች እንደሚከፋፈሉ ተገልጿል።

በተጨማሪም ከስድስት የተለያዮ ተቋማት እና ግለሰቦች ከ4 ሚሊየን ብር በላይ የሚተመን የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ ተደርገጓል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ  በዚሁ ወቅት፥ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ዙሮች ከመሰል በጎ ፈቃደኛ ተቋማት ግለሰቦች ያሰባሰበውን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ኮቪድ 19 መከላከል ተግባርና በበሽታው ምክንያት ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ማሕበረሰብ ክፍሎች ሲያውለው ቆይቷል ብለዋል።

ዛሬ የተደረገው ድጋፍም ለተመሳሳይ አላማ የሚውል መሆኑን በማንሳት ድጋፍ ያደረጉ ተቋማትን እና ግለሰቦችን አመስግለዋል።

በትዝታ ደሳለኝ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.