የባኔ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ”ማሮ” በዓል እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባኔ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ ”ማሮ” በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቀይ አፈር ከተማ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች እየተከበረ ነው።
ከጥንት ጀምሮ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እየተከበረ ለዛሬው ትውልድ የተሸጋገረው የማሮ በዓል የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች እንዳሉት ተገልጿል።
በዓሉ የተጣሉ እርቅ የሚያወርዱበት፣ ለተቸገረ ድጋፍ የሚደረግበትና በአብሮነት የሚከበር መሆኑም ተጠቁሟል።
በማሮ ክብረ በዓል በብሔረሰቡ አባላት ትልቅ አክብሮት የሚሰጣቸውና “ጉድል” በሚል የሚጠሩት የባህል መሪዎች ችቦ በማቀጣጠል ለብሔረሰቡ አባላት ያዳርሳሉ።
ይህም “ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋገርን፤ የብርሃን ጮራ አየን፤አዲስ ዘመን ተቀበልን” የሚል አንድምታ እንዳለውም ይነገራል።
በክብረ በዓሉ ላይ የክልሉና የዞን የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የብሔረሰቡ ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።